Seid Ahmed
ከአስራ አንድ ዓመታት በፊት ደሀ ነበርን፡፡ ያጣን የነጣን፣ ሙልጭ ያልን ነጭ ድሆች. ከድህነታችን ከብደት የተነሳ ስንት ሰዓት ላይ እንደምንበላ ሳይሆን ስንት ሰዓት ላይ ርሀባች ጋብ እንደሚል ነበር ዘወትር የምናስበው፡፡ እኔና እህቴ ትምህርት ቤት፣ “አበበ በሶ ባላ የሚል ምሳሌ “ቲቸር' ሲናገሩ በመጎምጀት ምራቃችንን እንውጥ ነበር፡፡
ቤታችን ውስጥ አንድ የረገበ የሽቦ አልጋ፣ ሁለት የሳር ፍራሾችና አራት የተወላገዱ ኩርሲ ወንበሮች ብቻ እንደነበሩን ዛሬም ድረስ እናቴ ሳጥን ውስጥ ያሉት ታሪካዊ ፎቶዎች ያሳብቃሉ ፡፡ ግድግዳ ላይ ገና እንደተረገዝኩ የሞተ አባቴ ፎቶግራፍ የዘመን ጥቀርሻ እንዳወየበው በላስቲክ ተለብዶ ተሰቅሏል።
እንግዲህ ቤታችን ሁለት ክፍል ነበረች፡፡ አሁን የነገርኳችሁ የሳሎናችንን (ወጉ እንዳይቀር ይዞታ ነው፡፡ ወደጓዳ ስትገቡ ውስጣቸው የእንጀራ ላስቲክ ብቻ ያለባቸው ሁለት ትልልቅና አሮጌ የእንጀራ መሶቦች ታገኛላችሁ፡፡ ጠርዛቸውን በደህና ቀን አይጥ የቸረቸፈው !!
ሁለቱም ሁልጊዜ ባዶ ነበሩ (አይጦች ከልጆቻቸው ጋር በእነዚህ መሶቦች አጠገብ ሲያልፉ ለልጆቻቸው እንዲህ እያሉ ታሪክ የሚያወሩላቸው ይመስለኛል፡፡ “በድሮ ጊዜ በአያቶቻችን ዘመን፣ እነዚህ መሶቦች ውስጥ ተበልቶ የማያልቅ እንጀራ ነበር፡፡ የዛሬን አያድርገውና ለስንቱ የአይጥ ሰርግ ድግስ የበቃ - ወይ ጊዜ መሶብም እንደ ዓለማያ ሀይቅ ይደርቃል !
እናቴ ታዲያ አማኝ ናት፡፡ በየሦስት ቀኑ መሶቡ ውስጥ የሚቀመጡትን የእንጀራ ላስቲኮች እያጠበች አድርቃ ወደ መሶቡ ትመልሳቸዋለች፡፡ “በረከት ሲመጣ አዋጅ አያስነግርም፣ ድንገት ከተፍ ቢል ተዘጋጅተን መጠበቁ ደግ ነው” ትላለች፡፡ ይሄን መራር ስብከቷን አልወደውም - ግን ትንቢቷ ሰመረ፡፡
እናቴ ነብይ ነበረች፡፡ ደሀ ነብይ በቤቱ አይከበርም፣ እናትም ብትሆን !! አከበርናትም አላከበርናትም ትንቢቷ ሰመረና በረከት እንደመብረቅ ወረደብን፡፡ (ምናባቴ ልበል ታዲያ) በስድስት ወር ውስጥ
መካከለኛ ገቢ ካላቸው ጎረቤቶች ተርታ ተሰለፍን፡፡ ጎረቤቱ ጉድ ብሎ ሳያባራ፣ በዓመቱ ምን የመሰለ ቤት ሰራን - ባለ አምስት ከፍል ዙሪያውን በግንብ የታጠረ፡፡ አጥሩ፣ ሰው እንዳይመጣብን ሳይሆን፡ በለመደ እግራችን ልንቀላውጥ እንዳንሄድ ራሳችንን ከነበረ ልምዳችን መከለያ ይመስላል፡፡
በተለይ ገና ሀብታም እንደሆንን አካባቢ አኗኗሩን አንላመደው ብለን ተቸግረን ነበር፡፡ እንግዲህ የዚህ ድንገተኛ ለውጥ ምክንያቱ እህቴ ፈረንጅ ማግባቷ ነበር (ደግ ፈረንጅ)፡፡ እንዴት እንዳገባችው (ይቅርታ እንዳገባት) ላውራችሁ፡፡ ከትምህርት ቤት እየመጣች፣ ልክ ኡስማን ሱቅ አካባቢ ስትደርስ፣ ፈረንጁ መኪናውን ፉጭጭጭጭ አድርጎ አቆመና “ኦማይጋድ” በማለት የእህቴን ውብት አደነቀ፡፡
በበኩሌ የእህቴ ውበት የፈረንጅ መኪና ማስቆም ቀርቶ የራሷን ሳንቲም 'ሆጭ አድርጋ ከፍላ የምትሳፈርበት ታክሲ እንኳን እጇን ብትዘረጋ የሚቆምላት አይመስለኝም ነበር፡፡ ግን ምን ይደረግ፡ ፈረንጆች ነገራቸው ሁሉ ግራ ነው፡፡ መኪናውን እዛው ጥሎት እህቴን ተከትሎ ቤታችን ድረስ መጣ፡፡
እናቴ ለዕርዳታ የመጣ መስሏት፣ ከዓይኖቿ “ትራጄዲ' ብርሀን ለቀቀች፡፡ የመንደራችን እንግሊዝኛ አዋቂ (የእህቴም ወዳጅ ብጤ) ሲራጅ ተጠርቶ መጣና ፈረንጁ ምን እንደሚል ተረጎመልን፡፡ እሷን ማግባት እፈልጋለሁ ነው የሚለው አለ ቅር ብሎት - ወደ እህቴ እየጠቆመ፡፡
እናቴ ባለማመን፣ “ማንን እጅጋየሁን” አለች፡፡ (እህቴ እጅጋየሁ ነው ስሟ)
“አዎ...ሌላ ማን አለ ታዲያ እማማ አረጋሽ” ሲራጅ ተነጫነጨ (እህቴ ጋር ማታ ማታ እዛ እንጆሪዋ ዛፍ ስር ይቆሙ ነበር) እናቴ፣ አንዴ ፈረንጁን፣ አንዴ እህቴን ስታይ ቆየችና፣
ሲራጅ…ግን…#እንግሊዘኛ_በደንብ_ታውቃለህ ?” ስትል ባለማመን ጠየቀች፡፡ ፈረንጁ ግን ወደ እህቴ እየጠቆመ በተኮላተፈ አማረኛ “ኮንጆ...ኮንጆ‥” በማለቱ “ይሄ ሰው አምርሯል” አለች እናቴ፡፡ ያው ጉዳዩ የፈጀውን ጊዜ ፈጅቶ በአንድ ወር ውስጥ ተጋቡ፡፡
ይሄ ፈረንጅ (ይቅርታ የእህቴ ባለቤት) ታዋቂ የታሪክ ተመራማሪም ነበር፡፡ይሄን የሰማሁ ቀን፣ “እህቴ ከመክሳቷ የተነሳ ሉሲን መስላው ይሆን ብዬ አሰብኩ፣ ወይስ እህቴ ይሄን ሚስኪን ፒተር ማንትስ ምናምን አስነካችው…፡፡ከተማውን የሞሉት ቆነጃጅት ሁሉ ፒተርን ሲያዩ ተበድረው የሚስቁ፣ መቀመጫቸውን እንደባንዲራ የሚያውለበልቡ፣ እንደ አቦሸማኔ ሽንጣቸውን እየመዘዙ አማላይ ሊሆኑ የሚደክሙ ስለምን ለዓይኑ አልሞሉም ? ግዴላችሁም ይሄ ፒተር ጤነኛ አይደለም፤ ገዳይ ዘመን የሌለው አፅም ሲያገላብጥ፣ ተዘግቶ የኖረ ዋሻ ሲበረብር አንዳች ነገር ተጣልቶታል፡፡
አንዲት የከርዳዳ ፀጉሯ ቱማታ አዳማ ድረስ የሚሰማ፣ በመረገጥ ብዛት ሶሉ ተረከዙ ላይ የተሸነቆረ ነጠላ ጫማ የምትጎትት ሴት በልዕልት ሂሳብ የሚያሳይ፣ ሰይጣነ መነፅር ዓይኑ ላይ የለጠፈበት ነገር አለ፤ እንጂ እህቴ ላይ እንዲህ ሙጭጭ ባላለ፡፡ ሚስኪን ፒተር
ምስኪን ፒተር ቤት መቶ እዛች ጠማማ ዱካ ላይ ቁጭ ብሎ እህቴን ዓይን ዓይኗን ሲያይ በእውነት እንደ ስጋ ዘመድ አንጀቴ ይንሰፈሰፋል፡፡
እንግዲህ ይሄ ፈረንጅ አሁን ጠቅልሎ ከመውሰዱ በፊት ትምህርቷን እንድትጨርስ . ለሁለት ዓመት እዚሁ ተቀመጠች፡፡ ፒተር ታዲያ በየስድስት ወሩ እየመጣ ቤታትን ጥምቀት ከማድረጉም በላይ፣ ይሄን ዶላር ልኬ ልሙት አለ ! ይልካል፤ ይመነዘራል፡፡ ይልካል፡ ወላ በጥቁር፣ ወላ በነጭ ገበያ እየተመነዘረ ዓለማችንን አየን፡፡ ስልካችን ከጮኸ ጎረቤቱ አይይይይ..አሁን አብርሃም ወደ ባንክ ሊሮጥ ነው ይላል፡፡ ቤታችን እግር የጣለው ሰው ሁሉ በሞቴ አፈር ስሆን ተብሎ ተጋብዞ ነው የሚሄደው፡፡ የእንግዳ ማረፊያ፣ የአብርሃም ድንኳን " በየቀኑ ብቅ እያሉ የሚመፀወቱ የኔ ብጤዎችም ብዙ ነበሩ፡፡ አንዳንዶቹማ ደንበኛ ከመሆናቸው . “ስለመብርሃን ኢይሉም፡፡ የግቢያችንን በር ያንኳኳሉ፡ በቃ በልተው ጠጥተው ይሄዳሉ፡፡
እንደውም አንዱ የኔ ብጤ መመፅውቱን መብት አድርጎት፡ ምነው ዛሬ ጨዉን አሳነሳችሁት ብሎ እስከመቆጣት ደረሰ፡፡ ይሄው ሰውዬ ሌላ ቀን የጎድን አጥንት ስለተሰጠው አኩርፎ ሳያመርቅ ሄደ፡፡ እናቴ እንደገና ጠርታ፣ ወዙ የሚፍለቀለቅ ቅልጥም ሰጠችው፡፡ ደስ ብሎት፣ በከፋ የሚያይሽ ቅልጥሙ ይሰበር ብሎ መረቃት፡፡
ይሄ ሁሉ ርዝቅ ሲመጣ፣ ግቢያችንን በሞላው የበረከት ውሀ ድሎት ሲዋኝ፡ ደሀ ብር አያግኝ ሲቆጥር ይጥላል" እንደሚባለው የእህቴ ፀባይ ይቀያየር ጀመረ፡፡ ልብሷን ለባብሳ፣ ቦርሳዋን አንጠልጥላ ጧት የወጣች ማታ ትመለሳለች፡፡ ድሮ ከሰው የማይቆጥሯት ጎረምሶች ሁሉ እንደጥዋ ከስሯ አንጠፋ አሉ፡፡ እሷን ብለው ሳይሆን የፈረንጅ ሚስት ጋር ዋልን ለማለት፡፡
እጅግዬ፣ እጅግሻ፣ ጂጂ፣ ጃ፣ ጆ፣ ጅን፣ ጅንአድ (ካፒታሏን አይቶ ይሆን?) በቃ ስሟ ፍዳውን እየ፡፡ በዚህ ዘመቻ ፊታውራሪው ሲራጅ ነበር (ተከተለኝ ወደ እጅጋየሁ ልዘምት ነው…)፡፡ የእህቴ ድፍረት ገደቡን ጣሰና ጭራሽ አርግዛ ቁጭ፡፡ ደግነቱ በዚያ ዓመት የእናቴ አምላክ የፒተርን እግር ያዘው፣
እናቴ መጀመሪያ እርግዝናው ከፒተር መስሏት ነገር ልታበላሽ ነበር፡፡ "ለፒተር ንገሩልኝ ደስ ይበለው፣ 'ዓይንህን ባይንህ ልታይ ነው' በሉልኝ ምናምን...! ልጅቱ ስትወለድ ከፆታዋ በስተቀር ቁርጥ ሲራጅን !! (የመንደራችን ነገረኛ ሴቶች ግር ብለው ላንግዌጅ ትምህርት ቤት ተመዘገቡ ይሄን ጉድ ለፒተር ለመንገር !!) ጉዳዩ ተሸፋፍኖ፣ ተደባብሶ ሾላ በድፍን' - የስድስት ወር ልጇን ለእኛ ጥላ እህቴ አሜሪካ ገባች፡፡
ሕፃኗን እልም ያለ ገጠር የምትኖር አከስታችን ጋር ላክናት፡፡ ሲራጅ "የገጠሪቱ ኢትዮጵያ ሕፃናት የትምህርትና የጤና ዕድል የማግኘት ዕድላቸው አናሳ ነው" አለ...ሃሃሃሃ (ሰውየው አሉ ከሚስቱ ውጭ ፋጤ ከምትባል ሴት በድብቅ ወልዶ ልጁ ሞተ ብለው አረዱት፡፡ ሚስቱ ፊት እያለቅስ ነገር ቸገረው፡፡ ዝም አይል ነገር ልጁ ሆኖበት እና ምን አለ፣ “አጀብ አላህ የፋጤን ልጅ ትገልባት”) ሲራጅም ልጄን ገጠር አትላኩብኝ አይል ነገር ቸግሮት፣ ዝም አይል ነገር የአባት
አንጀት ሆነና፣ “አጀብ አላህ የገጠሪቱን ኢትዮጵያ ሕፃናት…” ብሎ አረፈው፡፡
ሄሎ አብርሽዬ ደርሻለሁ፡፡ ለሲራጅ ደርሻለሁ በልልኝ፡፡” እይዋት እንግዲህ እህቴ ከነስንክሳሯ አሜሪካ ላይ፡፡ እንደነገ ልትበር እንደ ዛሬ ማታ፣ በጓሮ በኩል እንጆሪው ዛፍ ስር ሲራጅ ጋር ቁጭ ብለው እያወሩ አየዋቸው፡፡ ሲራጅ እንባውን ሲጠርግ አየሁት፡፡ አሳዘነኝ፡፡ ለስንቱ ልዘን ?
ሲራጅ ጋራጅ እየሰራ እናቱን ይረዳል፣ እህቱን ያስተምራል፡፡ በፊት ደስ የሚል ቀይ ልጅ ነበር - መልከ መልካም፡፡ ጥቁርቁር ብሏል እሁን፡፡ በየበረሃው ተበላሽቶ የቆመ መኪና ተከትሎ ሲባዝን እንዴት አይጦቅር
እዚህ እንጆሪ ዛፍ ስር ሕፃን ሆነን ፣ እኔ፣ እህቴና ሲራጅ እቃቃ እንጫወት ነበር - ሲራጅ እና እህቴ ባል እና ሚስት ሆነው፡፡ ደግሞ ሲራጅ ከመብሰሉ ብዛት ወደ ጥቁርነት የሚያደላ ያሞከሞከ የእንጆሪ ፍሬ ለእህቴ ይሰጣት ነበር፡፡ ከፍ ስንል እህቴና ሲራጅ አይነ ውሀቸው አላምርህ ሲለኝ ብቻቸውን ተውኳቸው፡፡ ይሄው አሁንም እዛው ቦታ ላይ እህቴ በጋራጅ ስራ የፈረጠመው የሲራጅ ትከሻ ላይ ራሷን ጣል አድርጋዋለች - የሆነ ህልም ነገር ነበር የሚመስለው፡፡
በፊት በፊት፣ እናቴ ሳንቲም ይቸግራትና የዘወትሩን ቡና እንኳን ሳታፈላ በር ላይ ቁጭ ብላ ትተከዛለች፡፡ እህቴ ወጣ ትልና ቡና ዳቦ ምናምን ይዛ ትመጣለች፡፡ ቤታችን ትንሽ ፋሲካ ይሆናል፤ ደስ ብሎን እናድራለን፡፡ ይሄ ነገር አንዴ፣ ሁለቴ ሳይሆን ለዓመታት የተደጋገመ ነገር ነበር፡፡
ሲራጅ ብር እየሰጣት እንደሆነ እኔ አውቃለሁ፡፡ እናቴም ታውቃለች፡፡ ግን “ከየት አመጣሽው? ብላ እህቴን አትጠይቃትም፡፡ ድህነት ልጇን የመገሰፅ ድፍረቷን ሰልቦት !! ሲራጅ ለእኛ ቤተሰብ፣ በትላንትና እና በዛሬ መካከል የነበረ ድልድያችን ነበር፡፡ እዩት እንግዲህ የእንጨት ድልድዩን አፍርሰን የብረት ድልድይ ስንዘረጋ፡፡ ተመልከቱ አንዱን ወንዝ፣ ሁለት ጊዜ ስንሻገር፡፡ ሳንደፈር የኖርን ማለት ምንድን ነው፡፡ ምድራችንን ፎከረን ለተቀበልናቸው ባዕዳን ሚስቶቻችንን አልቅሰን እናስረክባቸዋለን፡፡ ኡፍፍፍ….ይሄ የነማን ጦርነት ነው - የሲራጅና የፒተር፣ የአበሻና የፈረንጅ፣ የጥቅምና የፍቅር፣ የብረት መዝጊያና የጭራሮ መዝጊያ፣ የህሊናና የሆድ፣ የነፍስና የስጋ ወይስ የሰውና የፈጣሪ?
ከአራት ዓመት በኋላ እህቴ መጣች አምሮባት (ፈረንጅ መስላ፣ “ሰው ማንን ይመስላል ቢሉ ኑሮውን)፡፡ አገር ምድሩን ጉድ ያስባለ መኪና፡፡ አንድ ቸኮሌት የመሰለ የሁለት ዓመት ሕፃን ልጅ - ይዛ መጣች፡፡
ባለ ምናምን ኮከብ ሆቴል ፒተር፣ እኔ፣ እሷ እና የሁለት ዓመት ከልስ ልጇ ምሳ እየበላን፣ ፒተር የራሱን ጨርሶ እጁን ሊታጠብ ሲሄድ፡፡ ልጁ ድከ ድክ እያለ አባቱን ተከትሎ ከዓይናችን እንደተሰወሩ፣ እህቴ ወደኔ ሰገግ ብላ፣ “አብርሽ ሲራጅ አሁንም ሰፈር ነው የሚኖረው?" አለችኝ
እፍረት በተቀላቀለበት ጉጉት፡፡ ያስታውቃል በሆዷ አፍናው የኖረችውን እሳት በሰው ስታምሰለስለው የኖረችውን ህመም ዛሬ ከእኔ ከወንድሟ ጋር ልትካፈለው እንደተነፈሰችው ሰው መስያት !!
እውነቱን ለመናገር ሲራጅን ረስቸው ነበር፣ “እኔንጃ ካየሁት ቆየሁ፡፡ የሆነ ሰዓት ላይ ግን ጀዝ ነበር” አልኳት በግዴለሽነት፡፡ ዩኒቨርስቲ ገብቼ ስለነበር በእርግጥም ካየሁት ሁለት ዓመት አልፎኝ ነበር፡፡ ለመጨረሻ ጊዜ ያየሁት ሰፈር ድንገት ከሥራ ሲገባ ነበር፡፡ ጅዝብ ብሎ ኮሌታው እና ሸሚዝ ጉልበቱ እና መቀመጫው ላይ የሳሳ ጅንስ ሱሪ በጥቁር ተረከዟ በተጣመመ በእጁ ባንጠለጠላት ፌስታል ሦስት ዳቦዎች ይዞ፣ “እሽ አብርሽ ሥራ ጥሩ ነው” አለኝ ተማሪ መሆኔን ረስቶታል፡፡ ደግሞ አይኔን ማየት አልፈለገም፡፡ እህቴ ያዘጋጀችውን ጉርሻ ወደ ሰሀኑ መልሳ ፍዝዝ ብላ ቀረች፡፡ የነተበ ጫማ፣
ፒተር ያመጣልኝን ስልክ እየጎረጎርኩ እህቴን ከትካዜዋ ጋር ረሳኋት፡፡ ፓ እንዴት ቀውጢ ስልክ ነው...!!
“እኔ የምልሽ ይሄ ስልክ ዋጋው ውድ ነው አይደል ?" አልኳት በማዳነቅ፡፡ እህቴ በትዝብት እያየችኝ፣ “ሰባት መቶ ዶላር...” አለችኝ ድምፅዋ ሻክሮ ነበር፡፡
“ወደኛ ብር ሲመነዘር….” ብዬ ሳሰላ…፡፡
“#ወደ_እኛ_ብር_ሲመነዘር_ሲራጅ_ለእማማ_ቡና_ብሎ_ከሚሰጠኝ_ሁለት_ብር_አይበልጥም፡፡ #ሲራጅ_ለአብርሽ_ብሎ_ይሰጠኝ_ከነበረው_እስክርቢቶ_አይበልጥም”
ብላኝ ወደ መታጠቢያ ቤቱ ሄደች ፒተርና ልጇ ታጥበው ሲወጡ እሷ ልትታጠብ ስትሄድ መንገድ ላይ ተላለፉ፡፡ ፒተር ፈገግ አለላት፣ እህቴ እንደማታውቃቸው ዝም ብላ አልፋቸው ሄደች፡፡
ሲራጅ እስክርቢቶ ይልከልኝ እንደነበር ትዝ አለኝ፡፡ ያኔ በልብስ፣ በጫማ፣ በደብተር መያዣ ቦርሳ ይበልጡኝ የነበሩ ሕፃናትን የማስቀናበት ብቸኛ ንብረቴ ሲራጅ ያመጣልኝ የነበረው ቀይ እስከርቢቶ ብቻ ነበር፡፡ ሙሉ ቀይ ቢክ እስክርብቶ፡፡
ስልኩን ጠረጴዛው ላይ አስቀምጬ ወደ መታጠቢያ ቤቱ በትካዜ አመራሁ፡፡ እህቴ እያለቀሰች ነበር፡፡ ከአሜሪካ በመጣልኝ ስኒከር ጫማ ሲራጅ የሚባል አራት ዓመት ተቀብሮ የኖረ ፈንጅ ረገጥኩ፡፡ ሲመቸን የምንረግጠውን አናውቅ ! ርግጥ አረኩት።
https://www.Facebook.com/Seidtec41
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ
Waaaw