ማንኳኳት ቀረልሽ
ስትመጪ እንዳይመስልሽ የሌለው የሄድኩኝ
በሬን ነቀልኩልሽ እንቺ ስለሌለሽ ቤቴን ስለናድኩኝ
ማንኳኳት ቀረልሽ
በር የለውም ቤቴ ግቢ እንደመጣሽ
የምት ገቢበት ነው ባለፈው ያስወጣሽ
የህይዎት በር ነኝ ያለው ያንቺ ጌታ
በር ልክ አይደለም የበር ቦታ ነው የሀቀኛ ቦታ
አየሽ
በር አይደለም ህይዎት
በርማ ይዘጋል ለጠላው ለናቀው
በርማ ክፍት ነው ላቀፈ ላሞቀው
በር ህይወት አይደለም የኔ እድል አምሳሉ
የበሩ ቦታ ነው ማንንም የሚሸኝ
ማንም የሚገባው ለፈቀደው ሁሉ
የበሩ ቦታ ነው የአፍቃሪሽ ልኩ
ቅርብ ነኝ ለማለት ስትሄጂ እየለኩ
ክፍት ቦታ መሆን፣ ባዶ ቦታ መሆን
የሄደን ጥበቃ ከመጠበቅ መጉደል
በርን ከፍተሽ ለሄድሽ በርን እንደ መንቀል
በሬን ነቀልኩልሽ እንዳትቸገሪ
መቸገር ስራው ነው የተጓዥ አፍቃሪ
ግቢ እንደ መጣሽ
በር የለውም ቤቴ ሳትቅለሸለሺ
ነቃቅየዋለው
ደሞ ዝግ ነው ብለሽ እንዳትመለሺ
#2 ሻረልኝ በቀሌ ሻረ የህይዎት ቂም
መኖሬን ጀመርኩኝ ቢስምላህ ሯህማን ረሂም
ታውቅያለሽ ግዝት ነው ክንድሽን መመኘት
አውቃለው ሐራም ነው ከኔ ጋር መገኘት
ዳሩ
ፍቅር ግዝት ላያውቅ ላይገደው ሀራሙን
ግድ የለም እቀፊኝ ሰዎች ናቸው እንጂ መላዕክት አያሙን
ነይ በይ ሳሚኝ አሁን
ገሀነምን ረስተን ከጀነት ተነስተን
የሰው ግዜ ጥለን የኔና አንቺን ብቻ ዘመን አንጠልጥለን
በባዶ መስመር ላይ በህቡዕ ስንፃፍ
መነፈፈቅ ሀድሳችን መተቃቀፍ ቅዱስ መፅኃፍ
ሁሉንም ዘንግተን በሁሉም ተትተን ብንፋቀር ግዜ
የሰከረው ዓለም ሰከነ ባንድ ግዜ
ፅጥ......እረጭ.....ጭጭ.....ዝም...እፍን....እፍንፍን
ነይና እቀፊኝ ሰው ሞትን ሲዘፍን
እንገንጠል ከሰው ዘፈን እንገንጠል ከሰው ጀማ
ልድረስ ለስቅለትሽ ድረሽ ለኔ ጁምዓ
እንስገድ ለዓለምሽ እንስገድ ለዓለሜ
ባፍቅርሽ አይደለ ያንቺን እስጥፋኖስ እኔም መሳለሜ
የሰው ጣጣ ትተን እየተፋቀርን እየተማመንን እድሜ ለፍቅራችን ሁልት ጌታ አመንን
ስብሃት ለኣብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ
ስብሃት ለአላህ ዓለምን ላቆመ ንጉስ
አንቺን ስላደኝ መስጊድና መቅደስ ሁለት ስለት አልኝ
በሰው መቅጠርያ ልክ የማትቆጠሪ
እንደ ሊቃውንትሽ በሰው መለክያ ልክ ከቶ ማትለኪ
ነይ ኣኑሪኝ እስኪ።
ገጣሚ ኤልያስ ሽታሁን
ይመችህ
ምላሽ ይስጡሰርዝ